የመጽሐፍ ቅዱስ ስም ሲነሳ ብዙ ሰዎች ብዙ ጥያቄዎች አላቸው፡፡ ጥያቄዎቹን ጠቅለል አድርገን ብናያቸው አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ለማወቅ ከመፈለግ አንጻር የሚጠየቁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግን ከክህደት የተነሳ የሚጠየቁ ናቸው፡፡ ከማወቅ አንጻር የሚጠየቁ ጥያቄዎችን በዚች ለተማሪዎች ተብላ በተዘጋጀችውና አነስ ባለችው የተማሪዎች ማስታወሻ ውስጥ ለመመለስ ሙከራ ይካሄዳል፡፡ ይህቺ የተማሪዎች ማስታወሻ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምንነት ብቻ የምትነግረን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ለማወቅ እንዴት አድርገን እንደምናጠናም የተለያዩ የአጠናን ዘዴዎችን ታስተምረናለች፡፡
ለዚህ ላለነው ትውልድ አማኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የመጨረሻ ግቡ በጌታ እየሱስ ክርስቶስ ድኖ፣ በመንፈስ ቅዱስ ወደ እየሱስ ክርስቶስ እያደጉ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ነው፡፡ እንደዚህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ ከእግዚአብሔር ቃል ጥናት በተጨማሪ ተግባራዊና የህይወት ልምምዶችን ስናካትት ነው፡፡ ይኸም ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ የህይወት ለውጥ ያመጣ ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱሰ ጥናት ውስጥ እግዚአብሔር አድርጉ ያለውን ማድረግ አታድርጉ ያለውን ደግሞ አለማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እውነት እኛን ወደ እግዚአብሔር መልካምነት እንዲለውጠን ለማድረግ ነው፡፡ ልብ በሉ መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ይለውጠናል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን እኛ አንለውጥም፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ የአጠናን ዘዴን ስንማር በየትምህርት ቀናቶቹ መጨረሻ ተማሪዎች ሳምንቱን ሙሉ የሚሰርዋቸው የቤት ስራዎች አሏቸው፡፡ በመጨረሻም የክፍል ፈተና ይኖራል፡፡ የቡድን ስራዎችም ይበረታታሉ፡፡
- Teacher: Leul Makonnen